ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ6ኛ ጊዜ አስመረቀ፡፡

ጥር 23/2013 ዓ.ም

ጋምቤላ – ኢትዮጵያ

ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌን ጨምሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ  የመንገዶች ፈንድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ረሽድ መሀመድ፣ የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፣ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደርና ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ታንኳይ ጆክ፣ የጋምቤላ ሕ/ብ/ክ/መንግስት ም/ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ክቡር አቶ ጁል ናንጋል፣ የጋምቤላ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ ክቡር አቶ ላክደር ላክባክ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡጁሉ ኡኮክ፣ ም/ፕሬዚዳንቶች፣ የሴኔት አባላት፣ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች ፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች በተገኙበት ጥር 23/2013 ዓ.ም በመደበኛውና በእረፍት ቀናት  በመጀመሪያና በሁተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን  ተማሪዎች ለ6ኛ ጊዜ አስመርቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡጁሉ ኡኮክ ዩኒቨርሲቲው በ27 የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውና ሴኔቱ ያጸደቀላቸው በቅድመ-ምረቃ በመደበኛው ወንድ 596 ሴት 389 ድምር 985 በእረፍት ቀናት ወንድ 169 ሴት 30 ድምር 199  በድህረ-ምረቃ ወንድ 40 ሴት 5 ድምር 45 በጠቅላላው 1 ሺህ 229 ተማሪዎችን አስመርቋል ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የሰፈነባት ሆና እንድትቀጥል እያንዳንዱ ሰው በእኩልነትና በወንድማማችንት መንፈስ ተጋግዞ ሀገራችን ከእያንዳንዳችን የምትፈልገውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን፣ የስራ ትጋትን፣ የሙያ ክብርንና ለህዝቦቿ የላቀ ፍቅርን ካሳየን ለዓለም የምትተርፍ ባለብዙ ፀጋ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ  የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጋምቤላ ሕ/ብ/ክ/ መንግስት  ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎ የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት ባደረጉት ያላሳለሰ ጥረት በ2007 ዓ.ም የተከፈተው ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞ የምርምር ስራዎችን በመስራትና ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠናዎችን በማመቻቸት ከሀገራዊ ተልዕኮው ጎን ለጎን በአካባቢው ችግሮች ላይም የጥናታዊ መፍትሄ መፍለቂያ እንዲሆን  በታሰበው መሰረት ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር፣በስራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና፣በመልሶ ማቋቋም፣ በክልሉ የሰላም እሴት ግንባታና በሌሎችም ድጋፍ እያደረገና የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ረሽድ መሀመድ በበኩላቸው ተመራቂዎች ያገኛችሁትን ሁለንተናዊ ዕውቀት በተግባር ለማዋልና ለሀገራችን ኢትዮጵያ የወደፊት ዕድገት የበኩላቸሁን አስተዋጽኦ በማድረግ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመዋጋት የሚያስችላችሁን አስፈላጊውን ትጥቅ ስለያዛችሁ በጉጉት ለምትጠብቃችሁ ሀገራችሁና ለህዝባችሁ ልማትና ሰላም እንደምታውሉት ሙሉ እምነት አለኝ በማለት መልዕክታቸውን ለተመራቂ ተማሪዎች አስተላልፈዋል፡፡

በጨረሻም ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ለተማሪዎች ህብረትና ለሰላም ፎረም አባላት በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋና ሰርተፍኬትና የማበረታቻ ሽልማት፣ከኮሎጆች፣ ፋካልቲዎችና  ከህግ ትምህርት ቤት  የላቀ ውጤት ላሰመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳልያ ሽልማት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ  ተመራቂ ተማሪዎች የሜዳልያና የዋንጫ የሽልማት ስነ-ስርዓት ከተካሄደ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር ተዘምሮ የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ፍፃሜ ሆኗል፡፡ ሙሉ የምረቃ ስነ-ስርዓቱን ለማየት ሊንኩን ይጫኑ

https://www.facebook.com/541629952535552/videos/434626504558149?tn=F

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *