Students’ Discipline Rules and Regulation

መግቢያ

ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ካሉት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን በማሰልጠን የተሟላ ስብዕና ያለው ዜጋ በማፍራት በሀገሪቱ ልማት፣ዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ስራ ወዳድና ሥራ ፈጣሪ ዜጋን በማፍራት ረገድ ትልቅ ኃላፊነት የወሰደ ተቋም ሲሆን ይህንን ታላቅ ኃላፊነትም ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም በጠንካራ የሥራ ባህል እና አመለካከት፣ብቃት ባለው እውቀት እና የሙያ ክህሎት የታነፁና በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በህግ የበላይነት የሚያምኑ፣ እና የተቋሙን ህግና ደንብ በሚገባ እንዲያከብሩ ይጠበቃል፡፡ ተማሪዎች ዋነኞቹ የተቋሙ ተጠቃሚዎች እንደመሆናቸው መጠን ተቋማዊ ህግ እንዲከበር ከማንም በላይ እንዲፈልጉና እንዲያስጠብቁ ይጠበቃል፡፡

በዚሁ መሰረት ተማሪዎች የአካዳሚክ ህግና ደንቦች እንዲያውቁ፤ የሚጠበቅባቸውን የስነ ምግባር መርሆዎችን አክብረው የመጡበትን ተልዕኮ እንዲመለሱ ለማድረግ እንዲቻል የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ይህን የሥነ-ምግባር መመሪያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ ቁጥር 650/2002 አንቀጽ 44 በተሰጠው ስልጣን መሰረት አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ

አጠቃላይ ድንጋጌ

 1. አጭር ርዕስ

ይህ መመሪያ “የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር –/2006” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 1. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ

 • “ሚኒስቴር” ማለት የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡
 • “ዩኒቨርሲቲ” ማለት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲና በሥሩ የሚገኙ የስራ ሂደቶችን የሚያቅፍ ነው፡፡
 • “የተማሪዎች ዲን” ማለት በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ዘርፍ ለተማሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት እና አጠቃላይ ሁኔታ የሚመራና የሚከታተል አካል ነው፡፡
 • “ሠራተኛ” ማለት በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ውስጥ በቋሚነት፣ ወይም በኮንትራት ወይም በጊዜያዊነት ተቀጥሮ የሚያገለግል መምህር፣ የአስተዳደር ወይም የጤና ባለሙያ ወዘተ ነው፡፡
 • “መመሪያ” ማለት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የሥነ ምግባር መመሪያ ነው፡፡
 • “ተማሪ” ማለት በዩኒቨርሲቲው ባሉ የትምህርት ፕሮግራሞች በቅደመ ምረቃ፣ ድህረ ምረቃ፣ በመደበኛ፣ በማታ፣ በእረፍት ቀናት ወይም በክረምትና በርቀት ትምህርት ፕሮግራም ተመድቦ በመማር ላይ ያለ ሰው ነው፡፡
 • “ተገልጋይ” ማለት የዩኒቨርሲቲውን የተለያዩ አገልግሎች የሚፈልጉ በግል ወይም በቡድን የሚቀርቡ ተማሪዎችን ያካትታል፡፡
 • “የሥነ-ምግባር ግድፈት” ማለት በዚህ መመሪያ ወስጥ የተጠቀሱትን የሥነ ምግባር ደንቦቸንና ህጎችን በሚደረጉ ጥሰቶች የሚደረግን አስተዋጽዖ፡
 • “ደንበኛ” ማለት የዩኒቨርሲቲውን አገልግሎት የሚሸምት ወይም ለዩኒቨርስቲው

አገልግሎት የሚያቀርብ ሰው ወይም አካል ነው፡፡

 • “የሥራ ኃላፊ ማለት” ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር ቀጥሎ በየደረጃው በኃላፊነት

ተመድቦ የሚሰራ የስራ ኃላፊ ነው፡፡

 • “የዩኒቨርሲቲው እሴቶች” ማለት የተቋሙ አመራር፣ ሰራተኞችና ማህበረሰብ

የተቀበላቸውና ወደፊትም ተቀባይነት የሚያገኙ ተቋማዊ እሴቶች ናቸው፡፡

 • “የጥቅም ግጭት” ማለት በተቋሙ የስራ መሪዎችና ሰራተኞች ወይም ተማሪ ወይም

ለዩኒቨርሲቲው አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በተዘዋዋሪ መንገድ በስራው ላይ ገንዘብ

ወይም ልዩ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ካለመግባባት የሚከሰት ወይም የሚፈጠር ግጭት ነው፡፡

 • “የተማሪዎች ማህበር” ማለት በተቋሙ ህግና ስርዓት የሚቋቋም የዩኒቨርቲው

ተማሪዎች ህብረት ነው፡፡

 • “አካዳሚክ ማህበረሰብ” ማለት በተቋሙ ውስጥ በመደበኛነት ወይም በጊዜያዊነት

በመማር ማስተማር እና በምርምር ተግባር ላይ ተመድበው የሚገኙ የትምህርት

ባለሙያዎችን ያቀፈ ነው፡፡

 • “የከፍተኛ ትምህርት” ማለት በሥነ-ጥበብ፣ በማህበራዊ ሳይንስና በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ የዲግሪ ፕሮግራሞች፣ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ የትምህርት አግባቦችን የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡
 • “የዩኒቨርሲቲው ሀብትና ንብረት” ማለት በዩኒቨርስቲው ለትምህርት አገልግሎት የሚውሉ መገልገያ   መሳሪያዎች፣ በተማሪዎች መኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚሰጥ እና በተጠቃሚው  የዩኒቨርሲቲው ህብረተሰብ እጅ ሥራ ላይ የዋሉና ከስራ ውጭ ሆነው በሚመለከተው ውሳኔ  ሰጪ አካል ከሀብትና ከንብረት ያልተቀነሱ የመንግስት ንብረትና ሀብት የሆኑትን ያካትታል፡፡
 • “የዲሲፕሊን ኮሚቴ” ማለት በዩኒቨርሲቲው የበላይ ኃላፊ የሚሰየም፣ዕውቅና የተሰጠው እና በተቋሙ ለሚፈፀሙ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ወይም ጥፋቶችን ከሚመለከተው የበላይ አካል ክስ ሲቀርብ መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ ለዪኒቨርስቲው የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ አካል ነው፡፡
 • “ሴኔት” ማለት የአካዳሚክ ትምህርትን በሚመለከት ውሰኔ የሚሰጥ የዩኒቨርሲቲው

ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ አካል ነው፡፡

 • “የበላይ አመራር” ማለት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶችን

የያዘ አካል ነው፡፡

 • “የበላይ ኃላፊ” ማለት የጋምቤላ  ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ነው፡፡
 1. የተፈፃሚነት ወሰን

ይህ የተማሪዎች የሥነ-ምግባር ደንብ በዩኒቨርሲቲው  በተለያዩ የትምህርት መርሀ- ግብር በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽን (በማታ፤ በክረምትና በርቀት ተከታታይ ትምህርት) እንዲሁም የአጭር ጊዜ የትምህርት ስልጠና በሚሰጣቸው ተማሪዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

 1. የሥነምግባር መመሪያው ዓላማ
 • ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የሥነ-ምግባር ደንቡን ለይተው እንዲያውቁና ከኢ-ሥነ-ምግባራዊ ድርጊቶች በመታቀብ በእውቀት፣ በክህሎት፤ በሙያ ችሎታና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ዜጎች ሆነው እንዲገኙ ለማድረግ ነው፡፡
 • ተማሪዎች በሚፈጽሙት የዲሲፕሊን ጉድለት ወጥነት ባለው መልኩ እንዲታረሙና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ወይም የማይታረም ተማሪ ከዩኒቨርሲቲው ለማስናበት ነው፡፡
 1. የጾታ አገላለጽ

በዚህ መመሪያ ውስጥ በወንድ ፆታ የተገለፀው የሴት ፆታንም ይጨምራል (ያጠቃልላል)፡፡

ክፍል ሁለት

የተማሪዎች መብትና ግዴታ

በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2002 አንቀፅ 37 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ተማሪ ከዚህ የሚከተሉት መብትና ግዴታዎች አሉት፡፡

 1. የተማሪዎች መብት
 • በመማርና በምርምር ሂደት በነፃነት እውነትን የመሻትና ሃሳብን በነጻነት በሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ የመግለፅ፣
 • በመማሪያ ክፍል፣ በተለያዩ ካምፓሶች ውስጥ በአጠቃላይ ለመማር አመቺ ሁኔታን የማግኘትና የመጠቀም፣
 • በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሰብዓዊ መብታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ የመኖር፣
 • በዩኒቨርሲቲው ጉዳዮች ላይ መድልዎ ወይም ትንኮሳ እንዳይደርስባቸው ተቋማዊና ህጋዊ ጥበቃ የማግኘት፣
 • በማንኛውም የመምህርና የተማሪ ግንኙነት ገፅታዎች ፍትሐዊ ተጠቃሚ የመሆን፣ ለመማር የሚያበረታታ መልካም ተቋማዊ ድባብን የማግኘት፣
 • ስለ አካዳሚያዊ ብቃታቸው በተደነገጉ መርሆዎችና በተቋሙ አካዳሚክ መመዘኛዎች መሰረት የመመዘን፣ ኢ-ፍትሃዊ ምዘና ሲፈፀም ቅሬታን በዩኒቨርስቲው አሰራር መስረት በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የማቅረብና በግልፅነት ፍትህ የማግኘት፣
 • ግልፅነት ባለው የአሰራር ሥርዓት በአካዳሚክ ሰራተኞች የስራ አፈፃፀምና በአካዳሚክ ፕሮግራሞች አፈፃፀም ግምገማ ላይ የመሳተፍና አስተያየት የማቅረብ፣
 • የምግብ፣ የመኝታ፣ የመጠለያና የህክምና አገልግሎት የማግኘት፣
 • በተመደቡበት የስልጠና መስክ ተገቢውን የትምህርት፣ ሥልጠናና አስተዳደራዊ ድጋፎች የማግኘት፣
 • በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል በዘር፣ በኃይማኖት፣ በጎሳ፣ በእምነትና በፆታ መድሎና መገለል ሳይደርስባቸው የመማር መብት፣
 • በግል የትምህርት ማህደር በቋሚነት የሚቀመጡ መረጃዎቻቸው በሚስጢር የመጠበቅ፤
 • የተማሪዎችን የጋራ ጥቅሞች በህጋዊ መንገድ እንዲጠበቁ በማስቻል አግባብነት ባላቸው ህጎች በተቋቋሙና የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች በአባልነት በሚያቅፍ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ማህበር የመገልገልና የመሳተፍ፤
 • በዩኒቨርሲቲው ደንብና ስርዓት መሰረት በህጋዊ መንገድ በዩኒቨርሲቲው ንብረቶች የመጠቀምና የመገልገል መብት ናቸው፡፡
 1. የተማሪዎች ግዴታ

ማንኛውም የዩኒቨርሲቲው ተማሪ የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩበታል፡፡

 • ተማሪው በክፍል የመገኘትና ትምህርቱን በሚገባ የመከታተል፣
 • የአካዳሚክ ሰራተኞችን እና መምህራንን የመማር ማስተማሩን ሂደቱ የመምራትና የመቆጣጠር ሥልጣንን ማክበር፤
 • በተመዘገቡበት ትምህርት የተቀመጡ የብቃት መመዘኛዎችን የማሟላት፣
 • የዩኒቨርሲቲውን ዓላማዎችና መሪ እሴቶች የማወቅና የማራመድ፣
 • በክፍል ውስጥም ሆነ ግቢ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው ህግ እና ደንብ የማክበር እና የሌሎችን

መብቶች የማክበር፣

 • በተማሪዎች አገልግሎት ዙሪያ በወጡ ድንጋጌዎች ላይ የተመሰረቱትን የዩኒቨርሲቲውን ደንቦችና መመሪያዎች ማክበር፣
 • ከማንኛውም ህገወጥ ድርጊትና ከኢ-ሥነ ምግባራዊ ድርጊቶች መቆጠብ፣
 • ከማንኛውም ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንዲሁም ከማንኛውም የተቋሙ ተማሪ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ህጋዊ መብቶቻቸውን ማክበር፣
 • በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ቅሬታን በማሰማት መፍትሔን መሻት፣
 • የዩኒቨርሲቲውን ንብረት በጥንቃቄ መያዝና በአግባቡ መጠቀም፣
 • የዩኒቨርሲቲውን ንብረት ለአደጋ ከሚያጋልጡ ድርጊቶች መቆጠብ፣
 • ተያያዥነት ካላቸው ከሌሎች ጥፋቶች የመታቀብ፣ ግዴታ ናቸው፡፡

ክፍል ሦስት

የሥነምግባር ግድፈቶች ቅጣት አወሳሰን

ምዕራፍ አንድ

በንብረት ላይ የሚፈጸሙ የስነምግባር ግድፈቶች

 1. የንብረትና የገንዘብ ስርቆት ወንጀል ሙከራ
 • በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚፈፀም ማንኛውም የንብረትና የገንዘብ ስርቆት ወንጀል ለመጀመሪያ ጊዜ ለተፈጸመ ጥፋት ንብረቱን ማስመለስ እና ለሁለት ዓመት ከትምህርት ማገድ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ  ንብረቱን ማስመለስና ተማሪውን ከዩኒቨርሲቲው ማሰናበት ነው፡፡
 • አንድ ተማሪ የሌላውን ተማሪ ሎከር/ቁምሳጥን ያለ ባለቤቱ ፈቃድ የከፈተ፤እቃዎች ለመበርበር ሙከራ ያደረገ እና የበረበረ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት የመጨረሻ የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለሁለተኛው ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሶስተኛው ለሁለት አመት ከትምህርት  ይታገዳል፡፡
 • ማንኛውም ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎች ዙሪያ ተሳታፊ ከሆነ (ማለትም የተሰረቀን እቃ ያቀበለ ወይም የተቀበለ) ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት ንብረቱን በማስመለስ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ  ንብረቱን በማስመለስ ተማሪው ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 1. በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ
 • የዩኒቨርሲቲውን ንብረትና የሌላ ተማሪ ንብረት ወይም ገንዘብ የወሰደ፣ ተውሶ ያልመለሰ፣ ብድር ተበድሮ ብድሩን ላለመለስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የወሰደውን ንብረት ወይም ገንዘብ እንዲመልስ ተደርጎ የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የወሰደውን ገንዘብ/ ንብረት አንዲመልስ ተደርጎ  የመጨረሻ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት  የወሰደውን ገንዘብ/ ንብረት እንዲመልስ ተደርጎ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ሆን ብሎ እና የአደጋውን ውጤት መገመት እየቻለ አደጋ ያደረሰ፣ የሰበረ፣ ያበላሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፍል ተደርጎ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፍል ተደርጎ ለሁለት ዓመት ከትምህት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የንብረቱን ዋጋ ግምት ከፍሎ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ሆን ብሎ ሳይሆን /ሳያውቅ/ አደጋ ያደረሰ፣ የሰበረ፣  ያበላሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፍል ማድረግና የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ2ኛ ጊዜ ተመሳሳይ ጥፋት  የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፍል ማድረግና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ3ኛ ጊዜ ተመሳሳይ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፍል ተደርጎ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቸልተኝነት በዩኒቨርስቲዉ ንብረት ላይ አደጋ ያደረሰ፣ የሰበረ ያበላሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፈል በማድረግ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ተመሳሳይ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የንብረቱን ዋጋ ግምት እንዲከፈል ሆኖ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ተመሳሳይ ጥፋት የንብረቱን ዋጋ ግምት አንዲከፈል ተደርጎ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. በግቢው ንብረቶች ላይ እና የተማሪዎች  መኝታ ቤት  ለሚፈጸሙ ጥፋቶች

 በግቢው ውስጥ ባሉ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አይቶ ለሚመለከተው የዩኒቨርሲቲው ኃላፊ ሪፖርት ያላደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለ2 ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡

 • ቆሻሻዎችን በኮሪደርና ባልተፈቀደ ስፍራ የጣለና ዶርሙን በንፅህና ያልጠበቀ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ  የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣  ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ብር 50 ይቀጣል፣ እንዲሁም ለ16 ሰዓት የጉልበት ስራ ይሰራል፡፡
 • በዶርም (መኝታ ቤት) ውስጥ እግሩን፣ አጁንና ፊትን የታጠበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ብር 50  ቅጣትና ለ8 ሰዓት የጉልበት ስራ ይሰራል፡፡ እንደዚሁም በእጅ መታጠቢያ ላይ እግሩን የታጠበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3ኛ ጊዜ ጥፋት የ1ዓመት ከትምህርት መገለል፣ ደግሞ የተገኘ ከሆነ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ፀጥታን የሚያውኩ ዘፈኖችንና ቪድዮ በመኝታ አካባቢ እና በመኝታ ቤት ውስጥ ሌላውን በሚያውክ መልኩ መዝፈን፣ ማዘፈን፣ መጨፈር፣መጮህና ድምፅ ማሰማት  የፈጸመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ቆሻሻ ነገሮችን ታንከር ውስጥ በመጨመር የውኃውን ንፅህና የበከለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ከጥፋቱ ጋር የተያያዘ መጪ እንዲከፍል ተደርጎ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ከጥፋቱ ጋር የተያያዙ መጪዎችን እንዲከፍል ተደርጎ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በዶርም ውስጥ ንፅህናን ካለመጠበቅ የተነሳ በመጥፎ የእግርና የአካል ሽታ የሌላውን ተማሪ ጤንነት የረበሸ ወይም ተፅዕኖ ያሳደረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያልተፈቀዱ የዩኒቨርሲቲውን መገልገያ መሳሪያዎች/ንብረቶች ወደ መኝታ ክፍሎች ውስጥ ያስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በህንፃ ውስጥ የሚገኙ የገላ መታጠቢያ ክፍል ሲንኮችን ለልብስ ማጠቢያነት ወይም ለእግር መታጠቢያነት የተገለገለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በዶርም ውስጥ ልብሶችን ያጠበ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በአንድ አልጋ ላይ ለሁለት የተኛ እያንዳንዱ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በመስኮት መውጣትና መግባት በመስኮት መስታወት ላይ ወይም በሌላ ግድግዳ ላይ ያልተገቡ ፅሁፎችን የለጠፈ፣ የፃፈ ወይም የሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለፈቃድ ዶርምና መኝታ የተቀያየረ ወይም የተለዋወጠ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ፍራሽና ትራሶችን በመቦጫጨቅና በመቁረጥ ለመወልወያና ለሌላ አገልግሎት ያዋለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አንድ ተማሪ በትምህርት ውጤት ማነስ ከተቋሙ ሲሰናበት ወይም በግል ችግር ሲያቋርጥ ወይም በዲስፕሊን ቅጣት ሲወገድ በ72 ሰዓት ውስጥ ግቢውን ለቅቆ ካልወጣ ለፖሊስ ሪፖርት ይደረጋል፣ ከዚያም በግቢው በኃይል እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
 • በዓመቱ መጨረሻ ከዩኒቨርሲቲው የተረከበውን ንብረቶች ሳያስረክብ እና ህጋዊ ክሊራንስ ሳይዝ ግቢውን ለቆ የሄደ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ከዩኒቨርሲቲው የተዋሱትን ወይም ወጪ ያደረጉትን የስፖርት ማቴሪያል እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በጊዜና ንጽህናው በጠበቀ መልኩ ተመለሽ ያላደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለ ህጋዊ ፈቃድ ከሌላ ካምፓስ ወይም ተቋም ጓደኛን ወይም ዘመድ በዶርም ውስጥ ያሳደረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በመኝታ ክፍል ውስጥ ህጋዊ ያልሆኑ ፅሁፎችን፤ የሰውን ስብዕና የሚጎዱ መጽሄቶችን በማምጣትና ይህንኑ በማባዛት ሌሎች እንዲያነቡት ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የሚፈፀሙ ጥፋቶች

የኤሌክትሪክ ኃይልን ላልተፈቀደ ጉዳይ የተጠቀመ (ዶርም ውስጥ ምግብ ያበሰለ፤ሻይና ቡና ያፈላ… ወዘተ) ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡

 1. በተማሪዎች መኝታ ቤት አጠቃቀም የሚከሰቱ ጥፋቶች
 • ተደራራቢ አልጋዎችን የለያየ፤ ፍራሽና ትራስ መሬት ላይ ያወረደ፣ ውሃና ቆሻሻዎችን ያለ ቦታ የደፋ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ቲቪ ወይም ዲ. ኤስ. ቲቪ. ለመክፈትና ለመዝጋት የተመደበውን ኃላፊ ወይም የብሎክ ተጠሪ ሳያስፈቅድ ለግል ፍላጎት የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • መጸዳጃ ቤት፤ ኮሪደር፤ ዶርም፤ የብሎኮችን ዙሪያ ግድግዳና የበረንዳ ወለል በማንኛውም ዓይነት ነገር ያቆሸሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ባልተፈቀዱ ቦታዎች የታጠበ፤ ልብስ ያጠበ ፤ከሌሎች ክፍሎች ንብረት ያንቀሳቀሰና የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በውጭና በውስጥ የህንፃ ግድግዳዎች ላይ ማንኛውንም ዓይነት ጹሑፎችን የጻፈ ወይም የለጠፈ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለ2 ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በመጠጥ ውሃ ሲንኮችና ታንከሮች አካባቢ ወይም ውስጥ አስነዋሪ ነገር ያደረገ ማለትም አክታ የተፋ፣ የተናፈጠ ወዘተ ወይም ሌሎች እንዳይጠቀሙበት ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. የዩኒቨርስቲውን ሀብትና ንብረት በአግባቡ አለመጠቀም
 • የውኃ ቧንቧ ከፍቶ የተወ፤ ውሀው ሲፈስ በቸልተኝነት አይቶ ያለፈ፤ መብራት በቀን አብርቶ የወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በመታጠቢያ ሲንኮችና የሽንት ቤት ፈሳሽ መውረጃ ውስጥ ደረቅ ቆሻሻ የጣለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ቆሻሻውን እንዲያጸዳ ማድረግ ወይም የተያያዙ ወጪዎችን እንዲከፍል እና የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የተያያዙ ወጪዎችን እንዲከፍል ሆኖ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የተያያዙ ወጪዎችን እንዲሸፍን ሆኖ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በጠረጴዛዎች፣ የወንበርና የአግዳሚ መደገፍያዎች ላይ የተቀመጠ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ባልተፈቀዱ ቦታዎች መጸዳዳት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ አካባቢውን እንዲያጸዳ ማድረግና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ አካባቢውን እንዲያፀዳ ማድረግና ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ አካባቢውን እንዲያፀዳ ማድረግና ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. የተመራቂ ተማሪዎች የዲሲፕሊን ግድፈት
 • ተመራቂ ተማሪዎች የተዋሱትን ጋዋን በተሰጠው ጊዜ ገደብ የማይመልሱ ከሆነ በያንዳንዱ ቀን የተቀመጠውን ቅጣት ከፍሎ የተዋሰውን ጋዋን ያለምንም ብልሽት   እንዲመልስ ይደረጋል፡፡
 • በንዑስ አንቀጽ አንድ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ጋዋን እስኪመልስ ወይም ግምቱን እስኪከፍል የትምህርት ማስረጃው አይሰጥም፡፡
 • የመመረቂያ ጋዋን የጣለ ወይም ከጥቅም ውጭ ያደረገ ተመራቂ ከብር 50 (ሀምሳ ብር) ቅጣት ጋር የጋዋኑን  ግምት በገንዘብ ይከፍላል
 • የመመረቂያ ጋዋን ተውሶ የቀደደ ወይም አቆሽሾ የመለሰ ከብር 50 (ሃምሳ ብር) ቅጣት ጋር ጋዋኑን ሲወስድ በነበረበት ሁኔታ እንዲመልስ ይደረጋል፡፡

ምዕራፍ ሁለት

የማጭበርበርና የማታለል የስነምግባር ግድፈቶች

 1. የማታለል ወንጀል መፈፀም /DECEPTION/
 • በሌላ ተማሪ መታወቂያ መፅሐፍትና ሌሎች ንብረቶች የተዋሰና ለሌላ ተማሪ መታወቂያ ያዋሰ፣ ወይም ምግብና ሌሎች አገልግሎት እንዲጠቀም ያደረገ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜው ተመሳሳይ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ማስረጃዎችንና ሰነዶችን የደለዘ፣ የሰረዘ፣ አስመስሎ የፈረመ፣ የተጭበረበረ ማስረጃ ያቀረበ እንደሆነ  ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፤ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ  ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፤ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ባልተፈቀደ መግቢያና መውጫ የገባ ወይም የወጣ፣  ሌላን ግለሰብ ወደ ግቢ ለማስገባት የሞከረ፣ እንዲገባ ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት አንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜው ጥፋቱ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የሄደበትን ሳያሳውቅና ከፕሮክተሮች ፈቃድ ሳይጠይቅ ከዶርም/ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ውጪ ያደረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ እና ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የመጨራሻ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ሲሆን ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈጽመው ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በሌላ ተማሪ መታወቂያ ካርድ በመጠቀም ልዩ ልዩ የበር መግቢያና የቤተ መፃህፍት አገልግሎቶችን ያገኘ፣ ለማግኘት የሞከረ፤ ሌሎች ንብረቶችን ያዋሰ፣ የተጠቀመ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት አንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. አካዳሚክ ነክ ጉዳዮችን ማጭበርበር፤ ማታለልና ስርቆት መፈጸም /PLAGIARISM/
 • የሌላውን ተማሪ የቤት ስራና የቡድን ሥራ ኮፒ (ቅጅ) ያቀረበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ሲሆን ውጤቱም 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና ውጤቱን 0% ይደረጋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ጥፋቱ አንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የሌላውን ተማሪ ፈተና መቅዳት ወይም ማስቀዳት ወይም የክፍል ስራ ኮፒ (ቅጅ) ማቅረብ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠትና ውጤቱን 0% ማድረግ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት አንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ሆን ብሎ ወይም አስቦበት የሌላውን ተማሪ አካዳሚክ ዶክመንቶችን፤ፅሁፎችን፤ ደብተሮችንና መረጃዎችን ያበላሸ፣ የደበቀ፣ ወይም መሰል ተግባራትን የፈጸመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ተመጣጣኝ ንብረት እንዲተካ/እንዲመልስ ተደርጎ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣  ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የውጪ ወይም የዩኒቨርሲቲውን ተቋሙን ተማሪ በመጠቀም ፈተና ህጋዊ ባልሆነ መታወቂያ እንዲፈተኑለት ያደረገ፣ የተፈተነ፣ እንዲሁም ያስፈተነ ወይም የቡድን (Group Work) ስራዎችን ያሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ታግዶ ውጤቱ 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት  አንዲታገድ ተደርጎ ውጤቱ 0% ይደረጋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት  ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡ በዚህ መልኩ የተሳታፊው ግለሰብ በትምህርት ዘመኑ (ባች) የሚበልጥ ከሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገኝ ለአንድ አመት ይቀጣል፤ ለሁለተኛ ጊዜ ሲገኝ ለሁለት አመታት ከትምህርት ገበታው ይታገዳል፡፡
 • የተለያዩ የማታለል ዘዴዎችን በመጠቀም ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም በመስጠት ወይም በመቀበል ወይም በየትኛውም ዘዴ የማይገባን አካዳሚያዊ ጥቅም ያገኘ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና ያገኘውን ጥቅም እንዲያጣ ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • “ጎበዝ” ተማሪዎችን በኃይል በማስፈራራትና በማስገደድ የፈተና መልስ የተቀበለና ፈተናውን የሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ታግዶ ውጤቱ 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት  ታግዶ ውጤቱ 0% ይደረጋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ፈተና ወጥቷል በማለት የሀሰት ቅስቀሳና የሀሰት ወሬ ያሰራጨ ወይም የፈጠረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ 3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት  ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ከፈተና አዳራሽ ፈተና ወረቀት ደብቆ ወይም ትርፍ ፈተና ሰርቆ ይዞ የወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በፈተና አዳራሽ የፈተናውን ሂደት ለማወክ ሆን ብሎ ረብሻና ውዝግብ የፈጠረ ወይም ስነ-ስርዓትን ሣይጠብቅ ከፈተና ስፍራ የወጣ ወይም ለመውጣት የሞከረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በፈተና አዳራሽ የማይገቡና ያልተፈቀዱ አጫጭር መጣጥፎችና ፁሑፎችን ይዞ ፈተና ሲሰራ የተገኘ ወይም ለሌላ ያቀበለና ፈተናውን የሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ውጤቱም 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቡድን በመደራጀት ወይም በመረዳዳት ፈተና በመስራት በሌላው ተማሪ ውጤት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና ውጤቱም 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ሌላ ተማሪ የሰራውን የምረቃ ጽሑፍ /Senior Paper/ የሥራ ላይ ልምምድ ሪፖርት /Practical Attachment report and term  paper/ የራስ አስመስሎ ገልብጦ ምሁራዊ ስርቆት /plagiarism/ የፈጸመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ታግዶ ውጤቱም 0% ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ታግዶ ውጤቱም 0% ይደረጋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በፈተና ጊዜ ልዩ ልዩ መገልገያ መሣሪያዎችን /ካልኩሌተር፤ እስኪርብቶ፤ በሞባይል ቴሌፎን፤ ማስታወሻ ደብተር ወዘተ…/ ያለፈቃድ የተቀባበለ ወይም የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ከተማሪው የፈተና ውጤት ላይ 50% ይቀነሳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ከውጤቱ 100% ይቀነሳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ አመት ይሰናበታል፡፡
 • ፈተና ከተጀመረ በኋላ ፈተናውን አንብቦ/ተመልክቶ እንደ አመመው ሰው በማስመሰል ፈተናውን ጥሎ መውጣቱ በሀኪም ማስረጃ ሲረጋገጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ የፈተና ውጤቱ 0% ሆኖ የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ውጤቱ 0% ሆኖ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ውጤቱ 0% ሆኖ ለአንድ ዓመት ይታገዳል፡፡
 • ለፈተና የተሰጠው ሰዓት መጠናቀቁን ከተነገረ በኋላ ፈተናውን ሲሰራ የተገኘ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ከፈተናው ውጤት 5% ይቀነስበታል፤ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ከፈተና ውጤቱ 33.3% ይቀነስበታል፣ ለሶስተኛ ጊዜ ጥፋት ከፈተና ውጤቱ ላይ 50% ይቀነስበታል፡፡
 1. የማስመስል ድርጊት /Simulation Acts/
 • ተማሪ ሳይታመም ወይም የታመመ በማስመሰል ከክሊኒክ ሄዶ ህክምና የወሰደና መድሐኒቶችን በማውጣት የሸጠ ወይም የለወጠ ወይም ለሌላ አካል አሳልፎ የሰጠ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ከባድ ህመም ሳይገጥመው ወደ ከፍተኛ የህክምና ተቋም (Refer Letter) ደብዳቤ እንዲፃፍለት ያስገደደ፤ የሀሰት የህክምና ማስረጃ የጠየቀ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ሳይታመሙ የሀሰት የህክምና ማስረጃ የጠየቀ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለ2 ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • መታወቂያ ካርድና የመመገቢያ ካርድ (Meal Card,) ሳይጠፋበት እንደጠፋበት በማስመሰል ሌላ ተጨማሪ መታወቂያ (ID) ካርድ ያወጣ እና በሁለት መታወቂያ የተቋሙን አገልግሎት ያገኘ ወይም ለሌላ ተማሪ እንዲጠቀም ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ከተማሪዎች መማክርትና ማህበር ህጋዊ ውክልና ሳይሰጠው በተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች ማህበሩን በመወከል የተንቀሳቀሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡

ምዕራፍ ሦስት

የድብደባ፣ዘለፋና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሰላም ላይ

 የሚፈጸሙ የስነምግባር ግድፈቶች

 1. የድብደባና ዘለፋ ሙከራና ድርጊት እንዲሁም ስራን ማወክ
 • አንድ ተማሪ መምህራንን፤ ሰራተኛን እና ተማሪን የደበደበ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛው ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፤
 • የሥራ ክፍል መሪን፤ መምህርንና ሰራተኛን የተሳደበ፣ የዘለፈ፣ የዛተና ያስፈራራ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት የመጨረሻ የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለሁለተኛው ጊዜ ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜው ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የግቢውን ተማሪ የተሳደበ፣ የዘለፈ፣ የዛተና ያስፈራራ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት የመጀመሪያ የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለሁለተኛው ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ3ኛ ጊዜው ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በድብደባ ወንጀል ጥርስ ያወለቀ፤ በዓይንና በሌሎች የሰውነት አካላትን ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ተማሪ ያረሰው ጥፋት በፖሊስ እንዲመረመር ተደርጎ ጥፋቱ በማስረጃ ከተረጋጠ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ ጉዳዩም አግባብ ባለው ፍርድ ቤት እንዲታይ ይደረጋል፡፡
 • በመማሪያ ክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት የሚያውክ ተግባር መፈጸምና ከሚፈጽሙት ጋር መተባበር (በሞባይል፤ በካሜራ፤ በቪድዮ ካሜራ መምህራንን /ተማሪዎችን ቪድዮ መቅረጽ፤ ፎቶ ማንሳት…ወዘተ) ድርጊት የፈጸመ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜው ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜው ጥፋት ከዮኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ማንኛውም ተማሪ በግልም ሆነ በጋራ በመሆን የእምነት አኩልነትን በመጣስ የእምነት መፅሀፍቶችን የቀደደ፤ ለቆሻሻ መጥረጊያነት የተጠቀመ ወይም ያቃጠለ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ በህግም ተጠያቂ ይናሆናል፡፡
 • የዩኒቨርሲቲውን ንብረት ለከፍተኛ አደጋ በመዳረግ ለእሳትና ለኤሌክትሪክ ቃጠሎ መንስኤና ምክንያት በመሆን ጥፋት የፈፀመ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ ጉዳዩም አግባብ ባለው ፍርድ ቤት እንዲታይ ይደረጋል፡፡
 • ለመምህራንና ለሰራተኞች ብቻ በተዘጋጀ ላውንጅና መዝናኛ ቦታዎች የተጠቀመ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣  ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ  ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜው ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ  ይሰጠዋል፡፡
 • ማንኛውም ተማሪ ወይም የተማሪዎች ቡድን ከዩኒቨርሲቲው የሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳይሰጠው ለማንኛውም አገልግሎት ከተማሪዎች ገንዘብ የሰበሰበ ወይም የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ያዘጋጀ ወይም የተጠቀመ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ማንኛውም ተማሪ ባህላዊ እሴቶችን የሚጎዱ እና የተማሪውን ስብዕና የሚሸረሽሩ ፊልሞችንና ትዕይንቶችን ለሌሎች ተማሪዎች ወይም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ  በዩኒቨርሲቲው ግቢ ያሳየ እንደሆነ  ለመጀመሪያ ጊዜ ለፈጸመው ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ ለሁለተኛው ተመሳሳይ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ጥፋቱ ለሁለት ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፡፡
 1. ዘርን፤ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ሽፋን በማድረግ አመጽና ሁከት መፍጠር
 • ዘርን፤ሃይማኖትን እና ፓለቲካን ሽፋን በማድረግ ሁከት ለመፍጠር የሞከረ እና ይህም በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠ አንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱ ከዩኒቨርሲቲው  ይሰናበታል፡፡
 • ዘርን፤ ሃይማኖትንና ፓለቲካን ሽፋን በማድረግ ሁከትና ረብሻ የመፍጠርና አመፅ የመቀስቀስ ተግባር ላይ ተሰማርቶ የተገኘ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ዘርን፤ሃይማኖትንና ፖሊቲካን ሽፋን በማድረግ አመጽና ሁከት ከሚቀሰቅሱት አካላት ጋር የተባበረ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • አገራዊ ፋይዳና ጠቀሜታ የሌላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው እውቅና ያልሰጣቸው (የግል ልደት፤ ኤፕሪል ዘ ፉል፤ የእብደት ቀን፤ የህብረ-ቀለማት ቀን፤ የመሳሰሉት) ማክበርና ከሚያከብሩት ጋር የተባበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት የ24 ሰአታት የጉልበት ስራ አንዲሰራ ይደረጋል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የሌላ ተማሪን ወይም የዪኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ዘር፤ ሃይማኖት፤ ባህልና ማንነት ያንቋሸሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨረሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • የሀሰት ወሬ በማናፈስ ሁከት ያነሳሳ ወይም ረብሻ የፈጠረ ወይም አንዲፈጠር ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰበናታል፡፡
 1. አልኮል፤ ሀሺሽና ሌሎች አደንዛዝ ዕፆችን መጠቀም
  • ሀሺሽ እና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን የተጠቀመ፤ አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በእጁ የተገኘና ሌሎች እንዲጠቀሙ ያደረገ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትም/ት ማገድና የጥፋተኛውን ፎቶ መለጠፍ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ማሰናበት፡፡
  • አልኮል መጠጥ ጠጥቶና ሰክሮ ወደ ግቢ የገባ እና የሰላማዊ ተማሪዎችን ደህንነትና ፀጥታ ያወከ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት የጥፋተኛውን ፎቶ በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ይለጠፋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፡፡
  • በግቢው ውስጥ አልኮል መጠጦችን ይዞ የተገኘ ወይም ሲጠጣ የተያዘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ ለአንድ አመት ከትምህርት ታግዶ የጥፋተኛውን ፎቶ ይለጠፋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ታግዶ የጥፋተኛውን ፎቶ ይለጠፋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
  • ጉዳዩ በሚመለከተው አካል መታወቂያና ተገቢውን የማንነት መረጃ ሲጠየቅ ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆነ ወይም የከለከለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
  • የተማሪዎች ክበብ ኮሚቴ አባል፤ የህብረቱ አባል ወይም የመማክርቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይም መሪ ሆኖ በተሰጠው ስልጣን አጋጣሚ በእጁ የገባን ገንዘብ ወይም ንብረት አጉድሎ ከተገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ገንዘብ እና ንብረቱ እንዲመልስ ተደርጎ የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ገንዘብ እና ንብረቱን እንዲመልስ ማድረግና  ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ገንዘብና ንብረቱን እንዲመልስ በማድረግ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
  • ሲጋራ ወይም ጫት ይዞ ለመግባት የሞከረ በግቢ ወይም በዶርም ውስጥ ሲጋራ ያጨሰ ወይም ጫት የቃመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፡፡
 2. ማስታወቂያ መለጠፍ ወይም መገንጠል
 • በግቢ ውስጥ የተለጠፈን ህጋዊ ማስታወቂያ የገነጠለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት  ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ህጋዊ ያልሆኑ እንዲሁም ለአመፅ የሚያነሳሱ ማስታወቂያዎች የለጠፈ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት  ከዩኒቨርሲቲው  ይሰናበታል፡፡
 • በግቢው ውስጥ የተማሪዎችን መልካም ስነ-ምግባር የሚያበላሹ ድርጊቶች ማለትም ገንዘብ አስይዞ ቁማር የተጫወተ ወይም ያጫወተ … ወዘተ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማጠንቀቂያ እና ለ16 ሰዓታት የጉልበት ስራ ማሰራት፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ከተፈቀደው የመግቢያና መውጫ ሰዓት ውጭ ወደ ግቢ የገባና የወጣ እንዲሁም ከፖሊስ ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ የፈጠረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. ህገ ወጥ አደረጃጀትን በሚመለከት
 • ያለ ህጋዊ ፈቃድ በዩኒቨርሲቲው አዳራሽና መማሪያ ክፍሎች ትርኢቶችን፣ ስብሰባዎችንና  ፕሮግራሞችን ያካሄደ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለ ህጋዊ ፈቃድ ክበባትን፤ማህበራትንና ድርጅትን መስርቶ የተንቀሳቀሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ ጉዳዩም በህግ እንዲታይ ይደረጋል፡፡
 • የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ደንብ (ህግ) በሚፃረር ሁኔታ ተማሪዎች በማደረጀት ሁከት በመቀስቀስ በዩኒቨርሲቲው ሀብትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ ጉዳዩም በህግ እንዲታይ ይደረጋል፡፡
 • ብሔራዊ አንድነትንና ስሜትን የሚጎዳና የሀገርን ደህንነት የሚነካ ድርጊት የፈጸመ ወይም ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ የተገኘ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ በህግ ፊትም ቀርቦ ይዳኛል፡፡
 • ህጋዊ እውቅና ባልተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ስም በግቢ ውስጥ የተደራጀና የተንቀሳቀሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡

ምዕራፍ አራት

ጾታ ነክ የስነምግባር ግድፈቶች

 1. ከተቃራኒ ፆታ ጋር የሚከሰቱ ችግሮች
 • ተቃራኒ ፆታን ወደ መኝታ ክፍል እንዲገቡ የፈቀደ ወይም በመኝታ ክፍል አብሮ የተገኘ ወይም ለረጅም ሰዓታት አንድ ክፍል ውስጥ ዘግቶ አብሮ የቆየ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ሁለቱም ተቃራኒ ፆታዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳሉ፤ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታሉ፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወሲብ ለመፈጸም የሚገፋፉና በሌሎች ተማሪዎች ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጊቶችን ያሳየ ማለትም የተሳሳመ የተሻሸና የመሳሰሉትን የፈጸመ ወይም ሲፈጽም የተገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ሁለቱንም ተቃራኒ ፆታዎች  ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳሉ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት  ሁለቱንም ተቃራኒ ፆታዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳሉ፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታሉ፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በፈቃደኝነት ወሲብ ሲፈጸሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ተቃራኒ ፆታዎች ሁለቱም ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታሉ፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በመሆን በምሽት ለወሲብ በሚያጋልጥ አሳቻ ወይም በድብቅ ስፍራ ከተያዙ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ሁለቱንም ተቃራኒ ፆታዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳለ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታሉ፡፡
 • በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ አንድን ሴት አስገድዶ የደፈረ ወይም ሙከራ ያደረገ ተማሪ ከዩኒቨርሲቲው አንዲሰናበት ይደረጋል፣ ጉዳዩም አግባብ ባለው ፍርድ ቤት እንዲታይ ይደረጋል፡፡
 • አንድ ወንድ ተማሪ በሴት ተማሪ ላይ የጾታ ትንኮሳ ያደረገ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋቱ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛው ጊዜ ጥፋቱ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛው ጊዜ ጥፋቱ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አንድ ወንድ ተማሪ ሴት ተማሪዎችን የተቸ፣ ያንጓጠጠ፣ ስም ያጠፋ፣ በሴትነታቸው እንዲያፍሩ፣ እንዲሸማቀቁ ያደረገ እንደሆነ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ ፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛው ጊዜ ጥፋቱ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛው ጊዜ ጥፋቱ  ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. ለተቃራኒ ጾታ ብቻ በተፈቀዱ መገልገያዎች መጠቀም
 • በተቃራኒ ፆታ መፀዳጃ ቤትና ሻወር ቤት የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለ ምንም ድንገተኛ አደጋ በተቃራኒ ፆታ ዶርም ያለፈቃድ የገባ ወይም የተገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡

 ምዕራፍ አምስት

በተማሪዎች ምግብ ቤት፣ክሊኒክ እና ቤተ መጽሐፍት

 የሚፈጸሙ የስነምግባር ግድፈቶች

 በተማሪዎች ምግብ ቤት የሚከሰቱ የሥነምግባር ጥፋቶች

 • የምግብ አገልግሎት ያለአግባብ በድጋሜ የተመገበ ወይም ለመድገም ሙከራ ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል የጥፋተኛውም ፎቶ ይለጠፋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በካፍቴሪያ ውስጥ ሌሎች ተማሪዎች እንዳይመገቡ የቀሰቀሰ፣ ያነሳሳ፣ ሁከት የፈጠረ፣ ያስተባበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በሀሰት ወይም በአሉባልታ (የጾም ምግብ ውስጥ ስጋ አገኘሁ፤ የሙስሊምና የክርስቲያን ምግብ ተቀላቀለ፤ ምግብ ውስጥ እንግዳ ነገር አገኘሁ፤ወዘተ በሚል)  ተማሪዎች በሚቀርብላቸው ምግብ ላይ እንዲጠራጠሩ ወይም ምግብ እንዳይመገቡ ያደረገና በድርጊቱ የተባበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው  ይሰናበታል፡፡
 • የምግብ ቁሳቁስ (ኩባያ፤ሳህን … ወዘተ) በአግባቡ ያልመለሰ፤ ምግብ የደፋ ወይም የጣለ ወይም በአግባቡ ያልተስተናገደ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያና ለ24 ሠዓት የጉልበት ስራ ማሰራት፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት  ለ1 ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለ ፈቃድ ወደ ምግብ ማብሰያ ክፍል የገባ ባልተፈቀደ ስፍራ ምግብ የተመገበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለ1 ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በምግብ አዳራሽ ውስጥ ተገቢ ባልሆነ ቦታ እጁን የታጠበ፤ የአዳራሹን መዝጊያና ጠረጴዛ የደበደበ እና ጩኸት ያሰማ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለ24 ሰዓት የተለያዩ ስራ እንዲሰራ ይደረጋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አልኮል መጠጥ ጠጥቶና ሰክሮ ወደ ምግበ ቤት፤ ክሊኒክና ላውንጅ የገባ፣ የጮኸ ወይም የረበሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የተማሪ መታወቂያ ካርድ ወይም የምግብ መመገቢያ ካርድ የሰረቀ እና በገንዘብ ስምምነት የተደራደረ እና ልዩ ልዩ ጥቅም ያገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርስቲው ይሰናበታል፡፡
 • የምግብ መመገቢያ ካርድን ለሌላ ተማሪ በገንዘብ በማከራየት አሳልፎ የሰጠ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት  ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ከዩኒቨርስቲው ይሰናበታል፡፡
 • የወደቀ የተማሪ መታወቂያ ካርድ፣ የተማሪ መፅሐፍ ወይም ቁሳቁስ በማንሳት ለግል መጠቀሚያነት ያዋለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ንብረቱን እንዲመልስ ማድረግና የመጨረሻ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ከትምህርት ተቋሙ በአካዳሚክ ወይም በዲስፕሊን ምክንያት በተባረረ ተማሪ መታወቂያ ካርድ ስም የምግብ አገልግሎት ያገኘ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለሁለት አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ያለ ፈቃድ ወይም ልዩ አስገዳጅ ምክንያት ሳይኖር ምግብ ወደ ዶርም ይዞ የሄደ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ብር 50 ይቀጣል፡፡
 • ከውጭ ልዩ ልዩ ምግብ ይዞ ወደ ተማሪዎች ከፍቴሪያ ገብቶ የተመገበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የምግብ ሰልፍ የመጠበቅን ሥርዓት የተላለፈ ወይም ሌሎች አንዲተላለፉ የተባበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ባልተፈቀደ በር ወደ ምግብ ቤት የገባ ወይም ለመግባት የሞከረ ለመጀመሪያ ጥፋቱ የመጀመሪያ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አስተናጋጅ አስኪሰጠው ሳይጠብቅና ሳይሰጠው በራሱ እጅ ምግብ የወሰደ ወይም ለመውሰድ ሙከራ ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጹሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የመጨረሻ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • የተመገበበትን ዕቃ በተዘጋጀው ቦታ ያልመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ አመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 1. በተማሪዎች ክሊኒክ የሚከሰቱ የሥነ ሥርዓት ግድፈቶች
 • የሐሰት የህክምና ማስረጃ ከተለያዩ የህክምና ተቋማት ያቀረበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • ተገቢ ያልሆነ የህክምና ማስረጃ መጠየቅና ከጤና ባለሙያ ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ የፈጠረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አንድ ተማሪ በህመም ወይም በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ አስከሬኑ ከተሸኘ በኋላ የዕለቱን የትምህርት ፕሮግራም ያስተጓጓለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በሚመለከተው የሕክምና ተቋም ካልተፈቀደ በስተቀር ምግብ ከምግብ ቤት ይዞ የወጣ ወይም ይዞ ለመውጣት የሞከረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ኃላፊነት በጎደለው ስሜት ሆን ብሎ የራስን በሽታ ወደ ጤናማ ሰው እንዲተላለፍ ያደረገ ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፣ በፖሊስ  ለህግ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡
 1. በቤተ መጽሐፍት፣ በላብራቶሪና በመማሪያ ክፍሎች  የሚፈፀሙ የሥነሥርዓት

    ግድፈቶች

 • በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ድምፅ ያሰማ፣ ድምፅ የሚያሰሙ ጫማዎችን በማድረግ የእግር ኮቴ ያሰማ፣ የሌሎችን ትኩረት በሚሰርቅ ሁኔታ የጋራ ውይይት ወይም ድምጽ ያሰማ፣ ሞባይል  ቴሌፎን ያልዘጋ  እና የማስቲካን ድምጽ እያሰማ ያኘከ እና ተመሳሳይ ድርጊቶችን የፈጸመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ሆን ብሎ የቤተ-መጽሐፍቱን መብራት በማጥፋት ተጠቃሚዎችን ያወከ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ከሚገኙ መጽሐፍቶች፣ መጽሔቶች እና ከተለያዩ ዶክመንቶች መካከል ገንጥሎ ወይም ቀዶ የወሰደ፣ በመጽሐፍቶች ላይ የተለያዩ አላስፈላጊ ጽሑፎችን የጻፈና ሥዕል የሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በቤተመጽሐፍት ውስጥ ለአገልግሎት የተቀመጡ መጽሐፍቶችን የደበቀና ሌሎች እንዳይጠቀሙ ያደረገ ለራሱ ብቻ የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቤተ-ሙከራ ውስጥ የማስተማሪያ ዕቃዎችንና ንጥረ ነገሮችን ሆነ ብሎ ለአደጋ የሚያጋልጡ ድርጊቶችን የፈጸመና ያበላሸ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በቤተ ሙከራ ውስጥ ለማስተማሪያነት የተቀመጠውን ዕቃ ያለፈቃድ ወስዶ የተጠቀመ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቤተ-መጽሐፍትና በቤተ ሙከራ አገልግሎት መስጫ ክፍል ውስጥ የተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ በብር 50 ይቀጣል፣ የ8 ሰአት የጉልበት ስራም ይሰራል፡፡
 • ኤሌክትሮኒክ የሆኑ ዕቃዎች የሙዚቃ (ሲዲ፣ ራዲዮ ወዘተ) በቤተመጽሐፍትና በቤተ ሙከራ ውስጥ የተገለገለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቤተ ሙከራ ውስጥ ለማስተማሪያነት በተቀመጡ ዕቃዎች ሳይፈቀድለት በግል የተገለገለ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ወደ ቤተመጽሀፍት፤ ወደ ቤተ ሙከራና ወደ መማሪያ ክፍልና ወደ ምግብ ቤት ለአገልግሎት የሚገቡ ተማሪዎች ነጠላ ጫማ ማድረግ፣ ከወገብ በላይ ሰውነትን የሚያሳይ አለባበስ እና በጣም ስስ የሆኑ ልብሶችን መልበስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • ከቤተ መጽሐፍት መጽሐፍ ተውሶ በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ያልመለሰ በቤተመጽሀፍት ህግና ደንብ መሰረት ይቀጣል፡፡
 • በምሽት በቤተመጽሐፍት ውስጥ መብራት በድንገት ሲጠፋ ሳይፈተሽ ለመውጣት የሞከረ፣ ሁከት የፈጠረና የቤተመጽሐፍቱን ህግ ያላከበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • በቤተመጽሐፍት ወንበርና ጠረጴዛ ላይ ማስቲካ የለጠፈ፣ ቆሻሻ ወረቀት በየቦታው የጣለ፣ ጠረጴዛ የደበደበ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የመጀመሪያ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፤ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፡፡
 • አስፈፃሚ አካላትን፣ የዲስፕሊን ኮሚቴውንና ምስክሮችን ያስፈራራ፣ የዛተ፤ የተሳደበና የኃይል እርምጃ ለመወሰድ የሞከረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በተከሰሰበት ጉዳይ የሀሰት ማስረጃዎችን ያቀረበ ወይም በሀሰት የመሰከረ፤ የዲሲፕሊን ኮሚቴን ሆነ ብሎ ያሳሳተ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በተማሪዎች መካከል በሚፈጠረው ግጭት ቀስቃሽና ተባባሪ የሆነና ፀብና ሁከት እንዲባባስ ያደረገ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • የተሳሳተ መረጃ ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የሰጠና ያሳሳተ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡
 • በዲሲፕሊን ኮሚቴ በኩል ለማስረጃነት በደብዳቤ ጥሪ ሲደረግለት ያልቀረበና ለመቅረብ ያልተባበረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ለአንድ ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ2ኛ ጊዜ ጥፋት ለሁለት ዓመት ከትምህርት ይታገዳል፣ ለ3ኛ ጊዜ ለሚፈፀም ጥፋት ከዩኒቨርሲቲው ይሰናበታል፡፡

ክፍል አራት

የስነምግባር ጥፋቶች እርምጃ አፈጻጸምና የቅሬታ አቀራረብ

ምዕራፍ አንድ

የዲሲፕሊን ኮሚቴ አወቃቀር

 1. የዲሲፕሊን ኮሚቴ

ዩኒቨርሲቲው የዲሲፕሊን ክስ አጣርቶ የውሳኔ ሃሳብ ለሚመለከተው የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ያቋቁማል፡፡

 1. የተማሪዎች የዲስፕሊን ኮሚቴ ስለማቋቋም
 • የዲሲፕሊን ግድፈት ፈጽመው ክስ የሚመሰረትባቸውን ተማሪዎች ጉዳይ መርምሮ በአንቀጽ 44 ላይ የተጠቀሱትን የዲሲፕሊን ቅጣቶች መሰረት ያደረገ የውሳኔ ሀሳብ ለአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት የሚያቀርብ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡
 • የዲሲፕሊን ኮሚቴው 6(ስድስት) አባላት ይኖሩታል፡፡እነዚህም አባላት የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ/ የተማሪዎች  ዲን—————————————————————–ሰብሳቢ

ለ/ ከተማሪዎች ጉዳይ ፈፃሚ አንድ ተወካይ—————————————-አባል

ሐ/ የስርአተ-ፆታ ጉዳይ ክፍል ተጠሪ————————————————አባል

መ/ ከተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት————————————————-አባል

ሠ/ ከሴት ተማሪዎች ማህበር አንድ ተወካይ ተማሪ——————————-አባል

ረ/ የህግ አገልግሎት ጽ/ቤት ተወካይ—————————————አባልና ፀሀፊ

ምዕራፍ ሁለት

የክስ አመሰራረት ስነስርዓት

 1. ስለ ክስ አመሰራረት

የዲሲፕሊን ኮሚቴው ክስን አጣርቶ የውሳኔ ሀሳብ ሊያቀርብ የሚችለው

 • ዩኒቨርስቲው በማንኛውም የዲሲኘሊን ጥፋት በፈፀመ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ላይ ጥቆማ ወይም አቤቱታና ቅሬታ ሲያቀርብ፣ወይም
 • ማንኛውም ጉዳዩን የሚመለከተው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ/ግለሰብ፣ ወይም
 • በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የችግሩ ወይም የጥቃቱ ሰለባ ወይም ተጠቂ የሆነ አካል ሲያቀርብ ይሆናል፡፡
 1. የክስ አቤቱታ ይዘት

አንድ የክስ አቤቱታ በጽሁፍ ሆኖ የሚከተሉት ዝርዝር ነጥቦች ሊኖሩት ይገባል

 • የተከሳሹ ስም
 • የጥፋቱ ዝርዝር
 • ጥፋት የተፈፀመበትን ጊዜና ቦታ
 • የተጣሰው የህግ ድንጋጌ
 • የማስረጀዎች ዝርዝር
 1. ተማሪው ከአንድ በላይ በሆነ ጥፋት የተከሰሰ እንደሆነ

ተማሪው ከአንድ በላይ በሆነ ጥፋት የተከሰሰ እንደሆነ እያንዳንዱ ጥፋት ተለይቶ በአንቀጽ

30 በንኡስ ከ/2-3/ በተመለከተው መሰረት መገለጽ አለበት፡፡

 1. ክስን ስለማሻሻል
 • በዲሲኘሊን ክስ ጽሁፍ ውስጥ የተገለፀውን የጥፋት ዝርዝር በሚመለከት መሰረታዊ የሆኑ ነጥቦች ላይ ስህተት ወይም ግድፈት መኖሩ ሲታወቅ የውሳኔ ሀሳብ ከመቅረቡ  በፊት በማናቸውም ጊዜ ክሱን ማሻሻል ይቻላል፡፡
 • በአንቀጽ 30 ቁጥር ከ1-4 መሰረት ክስ አቅራቢ ክስን ሊያሻሽል የሚችለው በራሱ ተነሳሽነት ወይም ክሱን በሚያጣራው የዲስኘሊን ኮሚቴ ጥያቄ  መሰረት ሊሆን ይችላል፡፡
 1. ክስ የሚቋረጥበት ሁኔታ

 በዚህ መመሪያ የተገለፁት ሁሉ ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ታሳቢ ተደርጎ የዲስኘሊን ክስ የቀረበበት የዩኒቨርሲቲው ተማሪ በማናቸውም ምክንያት ትምህርቱን ያቋረጠ እንደሆነ የክሱ መታየት ይቆማል፡፡

ምዕራፍ ሦስት

የክስ መስማትና የውሳኔ አሰጣጥ ስነስርዓት

 1. ክስን ስለማሳወቅ
 • የዲሲኘሊን ኮሚቴ ክስ የቀረበበት ተማሪ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ የክሱን ጽሁፍና

ማስረጃዎች ቅጅ አያይዞ የክስ ማስታወቂያ ይልክለታል፡፡

 • የክስ ማስታወቂያ ክሱ የሚሰማበትን ቦታ፣ ቀንና ሰዓት የሚገልጽ ሆኖ ክሱ  ከሚሰማበት ቀን ቢያንስ ከ1 ቀን በፊት ለተከሳሹ መድረስ አለበት፡፡
 • ተከሳሹ ሊገኝ ባለመቻሉ ወይም ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የክስ ማስታወቂያውን ለመስጠት ያልተቻለ እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ተለጥፎ 2 ቀናት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡
 1. የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ

በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 34 ንኡስ ቁጥር ከ1-3 መሰረት የክስ ጽሁፍ የደረሰው ተከሳሽ/ተማሪ

 • ክሱ በአዋጁ መሰረት በይርጋ የታገደ ከሆነ ወይም
 • ተፈፀመ የተባለው ድርጊት በዲሲኘሊን ሊያስከስስ የማይችል ከሆነ ወይም
 • በተከሰሰበት ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ውሳኔ የተሰጠበት ከሆነ ክሱ ሊታይ አይገባም በማለት መቃወሚያ ሊያቀርብ ይችላል፡፡
 1. በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ የሚሰጥ ውሳኔ
 • የዲሲፕሊን ኮሚቴው መቃወሚያውን የተቀበለው እንደሆነ ክሱ እንዲዘጋ ለዩኒቨርሲቲው የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል ወይም
 • መቃወሚያውን ያልተቀበለው ከሆነ ተከሳሹ ለቀረበበት ክስ መልስ እንዲሰጥ ያዘዋል፡፡
 1. የክስ መልስ
 • የዲሲኘሊን ክስ የቀረበበት ተማሪ ክሱን የሚያምን ወይም የሚክድ ከሆነ ይህንኑ በዝርዝር በመግለጽ መልሱን በጽሁፍ ያቀርባል፡፡
 • በንዑስ አንቀጽ አንድ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚቀርበው የክስ መልስ የሚከተሉት ዝርዝር ነጥቦች ይኖሩታል፡

ሀ/  በክሱ ስለተገለፀው እያንዳንዱ ድርጊት ወይም ጥፋት የሰጠውን መልስ፣

ለ/  ተከሳሹ እንዲታዩለት የሚፈልጋቸውን የመከላከያ ማስረጃዎች ዝርዝር፣

ሐ/ ተከሳሽ ከዘረዘራቸው የመከላከያ ማስረጃዎች መካከል በእጁ የሚገኙትን   የጽሁፍ ማስረጃዎች ቅጂ፣ የዲስኘሊን ኮሚቴው እንዲያስቀርብለት የሚጠይቃቸውን ማስረጃዎች፣ በማን እጅ እንደሚገኙ እና

መ/  የተከሳሹ ፊርማ ይኖረዋል

 • በማመን ወይም በመካድ ስለተሰጠ መልስ ተማሪው ክሱን በማመን መልስ የሰጠ እንደሆነ የዲስኘሊን ኮሚቴው ተጨማሪ ማጣራት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ካላገኘው በስተቀር የቀረበውን ክስና የተሰጠውን መልስ በመመርመር ክሱ በቀረበለት 3 ቀን ውስጥ የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
 • ተከሳሽ የጥፋቱን ድርጊት በመካድ መልስ የሰጠ እንደሆነ የዲስኘሊን ኮሚቴው የከሳሹንና የተከሳሹን ምስክሮች በመስማትና የጽሁፍ ማስረጃዎቻቸውን በመመርመር ክሱን ያጣራል፡፡
 1. ማስረጃ ስለማስቅረብ

የዲስኘሊን ኮሚቴው ተከሳሹ እንዲቀርቡለት የጠየቃቸውን የጽሁፍ ማስረጃዎች ቅጂ የሚመለከተው አካል እንዲያቀርብለት ሊያዝ ይችላል፡፡

 1. ምስክር ሰለመጥራት
 2. የከሳሽና የተከሳሽ ምስክሮች ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ የዲስኘሊን ኮሚቴው መጥሪያ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡
 3. በአንድ ወይም በተያያዙ ጭብጦች ላይ ቃላቸውን የሚሰጡ ምስክሮች በአንድ ጊዜ ተጠርተው ተራ በተራ እየቀረቡ እንዲሰሙ ይደረጋል፡፡
 4. የዲስኘሊን ኮሚቴው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በራሱ አነሳሽነት ተጨማሪ ምስክሮች ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል፡፤
 5. ምስክርነት ስለመስማት
 • የዲስኘሊን ኮሚቴውን ምስክሮችን የሚሰማው ተከሳሹና ከሳሽ በተገኙበት ይሆናል፡፡
 • የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ/1/ ድንጋጌ ቢኖርም የከሳሽ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ ተከሳሹ እንዲገኝ ተነግሮት በቀጠሮው ቀን ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ወይም የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ ከሳሽ እንዲገኝ ተነግሮት ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ምስክሮቹ ሌላው ተከራካሪ ወገን በሌለበት ሊሰሙ ይችላሉ፡፡
 • የዲስኘሊን ኮሚቴው ምስክሩ ከክሱ ጋር በተያያዘ ራሱ የሰማውን ወይም ያየውን ወይም የተገነዘበውን እንደዲያስረዳ እየጠየቀው የሚሰጠውን መልስ እንዲመዘገብለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
 • የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌ ቢኖርም ምስክሩን የጠራው ተከራካሪ ወገን ምስክሩን ተጨማሪ ጥያቄዎች መጠየቅና የሚሰጠው መልስ እንዲመዘገብለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
 • የከሳሽ ምስክሮችን ተከሳሹ፤ የተከሳሽ መከላከያ ምስክሮች ከሳሽንና የዲስኘሊን ኮሚቴው የጠራቸውን ተጨማሪ ምስክሮች ደግሞ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ፡፡
 • መስቀለኛ ጥያቄ የሚቀርበው ምስክሩ የሰጠው ትክክለኛ ያልሆነ የምስክርነት ቃል ካለ ይህንኑ ለዲስኘሊን ኮሚቴው በግለጽ ለማሳየት ነው፡፡
 1. የተከሳሽ የመጨረሻ ሀሳብ

 የዲስኘሊን ኮሚቴው ምርመራው ከመጠናቀቁ በፊት ተከሳሹ የመጨረሻ ሀሳቡን ለመስጠት  እንዲችል እድል ይሰጠዋል፡፡

 1. የምርመራ ሪፖርት
 • የዲሲኘሊን ኮሚቴው ምርመራውን እንዳጠናቀቀ የምርመራውን ውጤትና የውሳኔ ሀሳብ የያዘ ሪፖርት ለዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዘዳንት ክሱ በቀረበ 5 ቀን ውስጥ ያቀርባል፡፡
 • የምርመራው ውጤት የተከሳሹን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጥ ከሆነ የዲስኘሊን ኮሚቴው የሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ ሊወሰድበት የሚገባውን የቅጣት እርምጃ ማመልከት አለበት፡፡
 • የዲስኘሊን ኮሚቴው ቅጣትን በሚመለከት የሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ፡- የጥፋቱ ክብደትና ድርጊቱ እንዲሁም የተፈፀመበትን ሁኔታ፤ተከሳሹ ባለፈው የትምህርት ዘመኑ ያሳየውን መልካም ስነ-ምግባርና አጥጋቢ የስራ/የትምህርት ውጤት፤የተማሪውን የቀድሞ የጥፋት ሪከርድ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡
 • የምርመራው ውጤት የተማሪውን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጥ ካልሆነ ከክሱ ነፃ መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡
 1. የቅጣት አወሳሰን ስነስርዓት
 • የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ተመሳሳይ የስነ-ምግባር ግድፈቶችን ወይም ጥፋቶችን የፈጸመ እንደሆነ በዚህ መመሪያ በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሰረት ቅጣቱ ይፈጸማል፡፡
 • ተማሪው የተለያዩ ጥፋቶች ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ የፈጸመ ከሆነ በሌሎች አንቀጾች የተቀመጡትን የቅጣት እርምጃዎች መሰረት እንደ ጥፋቱ ክብደትና ቅለት ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
 • ይህ ድንጋጌ ተማሪው ቀደም ባሉት ጊዜያት የፈጸማቸው የስነ-ምግባር ግድፈቶች እንደ ማክበጃነት ከመውሰድ አያግድም፡፡
 1. የዲሲፕሊን ቅጣት ዓይነቶችና አመዳደብ
 • የዲሲፕሊን ጉድለት የፈፀመ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ እንደ ጥፋቱ ክብደት ዓይነት ከሚከተሉት ቅጣቶች አንዱ ሊወሰንበት ይችላል፡፡

ሀ) የመጀመሪያ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፤

ለ) የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፤

ሐ) የገንዘብ ቅጣት ወይም የጉልበት ስራ ማሰራት፤

መ) የአካዳሚክ ውጤት መቀነስ፤

ሠ) አንድ ዓመት ከትምህርት ማገድ፤

ረ) ለሁለት ዓመት ከትምህርት ማገድ

ሰ) ከዩኒቨርሲቲው ማሰናበት፤

ሸ) ከዩኒቨርሲቲው ማሰናበት እና ለፍርድ ቤት ማቅረብ፤

ቀ) የዕጩ ተመራቂው የትምህርት ማስረጃ ለሴምስተር፤ለአንድ አመት ወይም ሙሉ በሙሉ አለመስጠትና ዕጩ ተመራቂው ከዩኒቨርሲቲው ማሰናበትና እንደ ጥፋቱ ክብደት ታይቶ ለህግ ማቅረብ ናቸው፡፡

 • በአንቀጽ 29/1 ከ”ሀ” እስከ “መ” የተዘረዘሩት ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት ተብለው ይመደባሉ፡፡
 • በአንቀጽ 29/1 ከ”ሠ” እስከ “ቀ” የተዘረዘሩት ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣቶች ተብለው ይመደባሉ፡፡
 • አንድ ተማሪ በዲሲፕሊን ቅጣት ከተቀጣ በኋላ ቅጣቱ በሪከርድነት ሊያዝበትና ሊጠቀስበት ይችላል
 • በንዑስ አንቀጽ አራት የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ቅጣቱ በሪከርድነት ሊያዝ የሚችለው ቀላል የዲሲፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት፤ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት ከሆነ ትምህርቱን እስከ ሚያጠናቅቅበት ጊዜ ድረስ ይሆናል፡፡
 • ይህ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ግድፈት ፈጽሞ ከተገኘ ግድፈቱ/ጥፋቱ አሁን ለቀረበበት ክስ ቅጣት ማክበጃነት ይውላል፡፡
 1. የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ስልጣን
  • የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዘዳንት በዚህ መመሪያ በአንቀጽ ቁጥር 42 መሰረት የቀረበለትን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የኮሚቴውን የውሳኔ ሀሳብ ለማጽደቅ ወይም በቂ ምክንያት ሲኖረው በኮሚቴው ከቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ለመስጠት ወይም ኮሚቴው ጉዳዩን እንደገና እንዲመረምር ለማዘዝ ይችላል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ጉዳዩ በቀረበለት በ1 ቀን ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
  • በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት የተሰጠው ውሳኔ ለተማሪው በጽሁፍ መሰጠት አለበት፡፡ የተማሪው ጥፋተኝነት ተረጋግጦ ውሳኔ ከተሰጠ የተማሪውን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጠው ውሳኔ በዩኒቨርሲቲው የማስታወቂያ ሰሌዳ ተለጥፎ ለ5 ቀናት ይቆያል፡፡ ይህም የሚሆነው ጥፋቱ የመጨረሻ ውሳኔ ሲያገኝ ይሆናል፡፡
  • በከባድ የዲሲኘሊን ጥፋት ተከሶ በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ውሳኔ በተሰጠበት ጉዳይ ያልረካ ተማሪ ይግባኙን በ2 ቀናት ውስጥ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ማቅረብ ይችላል፡፡ ፕሬዝዳንቱ የቀረበለትን ይግባኝ መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔውን በ2 ቀናት ውስጥ ያሳውቃል፡፡ በፕሬዝዳንቱ የሚሰጠው የይግባኝ ወሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡
  • የዲሲፕሊን ቅጣት የማንኛውም ፍ/ቤት ውሳኔ ሳይጠበቅ ወይም ሳይከተል ሊወሰን ይችላል፡፡

ክፍል አምስት

ይግባኝ እና የአፈፃፀም ሂደት

 1. የይግባኝ መብት
 • አንድ አቤቱታ አቅራቢ ተማሪ በተቀጣበት ጉዳይ ላይ በመቃወም ይግባኝ ለሚመለከተው አካል በፅሁፍ የማቅረብ መብት አለው፡፡
 • ይግባኝ የሚቀርበው ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ሲሆን የቅጣት ውሳኔ በኮሚቴው ከተሰጠበትና ተከሳሹ ውሣኔውን ከሰማበት በሁለት የስራ ቀናት ውስጥ ብቻ አቤቱታ አቅራቢው በፅሑፍ የመከላከያና የተቃውሞ ሀሳቡን ሊያቀርብ ይችላል፡፡
 1. የይግባኝ አቀራረብና አፈፃፀም
 • የይግባኙ መሰረታዊ ፍሬ ነገር፤ መረጃዎች እና ደጋፊ ዶክመንቶች ተያይዘው ለቅሬታ ሰሚው ይቀርባሉ፤
 • ቀደም ሲል በዲሲፕሊን ኮሚቴው የተካሄደው የምርመራ ሂደትና ትክክለኛነት ይጣራል፤
 • ውሳኔው በተሟሉ መረጃዎች ላይ በመደገፍ መከናወኑንና ትክክለኛነቱ ይረጋገጣል፤
 • የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ በተማሪዎች የስነ-ምግባር ደንብ መሰረት መከናወኑ ይረጋገጣል፤
 • ሆኖም የቀድሞ ውሳኔ ሰጪው ኮሚቴ ከተመለከተው ማስረጃ ውጭ ሌላ አዲስና ተጨማሪ ማስረጃ ከተገኘና እውነታዎች በአግባቡ ቀርበው በትክክል ካልታዩ እንዲሁም ተከሳሹ እንዲያውቃቸው ካልተደረጉ  ቅሬታው እንዲታይ ይደረጋል፣
 • በዚህ መሰረት አዲስ ማስረጃ ከተገኘ ይግባኙ ተቀባይነት የሚያገኝ ሲሆን፣ የቀድሞው ውሳኔ እንዲሻሻል ወይም እንዲሻር የውሳኔ ሀሳብ ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ይቀርባል፤
 • ይግባኙ ለፕሬዚዳንቱ ቀርቦና ታይቶ እንዲሻሻል ወይም እንዲሻር በተደረገ  በ2 ቀናት  ውስጥ ውሳኔ ተሰጥቶበት ለተማሪዎች ጉዳይ ጽ/ቤት፤ለዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት እና ለሚመለከተው ክፍል ይገለፃል፡፡

 ክፍል ስድስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

 1. መመሪያው በስራ ላይ የሚውልበት ጊዜ፣

ይህ መመሪያ ከዛሬ ሚያዚያ —– ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል::

 1. መመሪያውን ስለማሻሻል

 ይህ መመሪያ እንደአስፈላጊነቱ በዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ እውቅናና ተቀባይነት አግኝቶ ሊሻሻል ይችላል፡፡

Share the contents abroad