News Detail
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የቢዝነስ ሀሳብ ፈጠራ ውድድር አካሄደ፤
ህዞብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (መጋቢት 20/2018 ዓ.ም)
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ባወጣው የውድድር ማስታወቂያ መሠረት የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸው መምህራን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የፌደራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዛሬው ዕለት ውድድር አካሂደዋል።
የውድድሩ ዓላማ የተሻለ የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸው መምህራን እና ተማሪዎችን በመለየት የገንዘብና ተከታታይ የሆነ የምክርና ስልጠና ድጋፍ ተደርጎላቸው የዩኒቨርሲቲውን የቢዝነስ ማፍለቂያና ማበልፀጊያ ማዕከል በማቋቋም ፈጠራዎችን ወደ ማህበረሰቡ በማውረድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው።
ውድድሩን በንግግር የከፈቱት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ እና ልዩ ረዳት ዶ/ር ጀምበሩ አለሙ እንደገለጹት ሀሳቦች በሀሳብ ደረጃ እንዳይቀሩ በዛሬው ዕለት በተዘጋጀው ውድድር ላይ ጥሩ የቢዝነስ ሀሳብ ያላችሁ መምህራን እና ተማሪዎች ፕሮፖዛላችሁን አቅርባችሁ ከተመረጣችሁ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ በማደረግ ወደ ስራ የምትገቡ ይሆናል ብለዋል።
ዶ/ር ጀምበሩ አክለው እንደገለጹት በዚህ ውድድር አሸናፊ ሆነው የሚመረጡ የቢዝነስ ሀሳቦች አስፈላጊው እገዛ እየተደረገላቸው ካደጉና ከተሻሻሉ በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ችግር የሚፈቱና ለፈጠራ ባለቤቶቹም ገቢ የሚያስገኙ ፈጠራዎች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ስልጠና የሰጡትንና ውድድሩን የዳኙትን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት እና ኢንዱስትሪ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ መኮንን እና መ/ር ሚኪያስ ብርሃኑን ከልብ አመስግነዋል።
የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር መ/ር ገብረእግዚአብሄር አሳየኸኝ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የተሰጠው ስልጠናና በመጨረሻም የተደረገው የቢዝነስ ሀሳብ ውድድር በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ጠቅሰው ቀደም ሲል የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማዕከል ተማሪዎች ያሳዩትን የነቃ ተሳትፎ አድንቀዋል።
በመጨረሻም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በእንደዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ለመስራትም ስራ ክፍላቸው ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
በመጨረሻም የቢስነስና ፈጠራ ኢንከዩቤሽን ስልጠና የወሰዱ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ከትላንት ጀምሮ ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና መምህራን እና ተማሪዎች በሚገባ የተከታሉ ሲሆን የቢስነስ ሀሳቦቻቸውን ወደ መሬት በማውረድ ለመስራት መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።