News Detail

ክስተቶች
Mar 12, 2026 259 views

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፤

ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (መጋቢት 3/2018 ዓ.ም)

በዓሉ የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተከብሮ ውሏል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር በጋምቤላ ክልል የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከልና የሴቶችን የውሳኔ ሰጭነትና የመሪነት ሚና በማሳደግ ረገድ በተከናወኑት ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አክለው ገልጸዋል።

የሴቶችን አቅም በማጎልበት የውሳኔ ሰጪነትና የመሪነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየተከናወኑ ላሉት ስራዎች መሳካት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶችን አቅምና የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ የላቀ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው ርዕሰ መስተዳደሯ አስገንዝበዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በብዙ መስኮች እጅግ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው ይህም ሴቶች በሀገራችን የልማት ጉዞ ውስጥ ያላቸውን ቁልፍ ሚና ያሳያል ብለዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገር ልማት ውስጥ እጅግ ከፍተና ሚና ያላቸው ተቋማት ሲሆኑ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሴቶች በትምህርት፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ውስጥ የማይተካ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ሴቶች በትምህርት፣ በምርምር፣ በአመራር እና በፈጠራ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በቀጣይነት እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አሪያት ኡጁሉ በበኩላቸው በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ፆታዊ ጥቃቶችንና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቅድስት ማሞ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።

በዕለቱ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ የ6 ወራት ስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች የውይት መነሻ ጽሁፎች የቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ፕሮግራሙን ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፣ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን አዘጋጅተዋል፡፡

የሴቶችን ቀን በማስመልከት በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የፌደራል መንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ቤተልሔም ኡሉማ፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቅድስት ማሞ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዲሪባ ኢቲቻና ሌሎችም በአኝዋሃ ዞን በአቦቦ ወረዳ በመገኘት አልዌሮ ግድብን ጎብኝተዋል።

በጎብኝቱም የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን፣ የአስተዳደር ሴት ሠራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ተገኘተዋል።

 

 

Recent News
Follow Us