News Detail
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከመምህራን እና ከሠራተኞች ጋር ውይይት አደረጉ፤
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኑነት (ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም)
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ከሠራተኞች እና መምህራን ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አካሂደዋል፡፡
የውይይቱን ዓላማ በማስተዋወቅ ያስጀመሩት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ እንደገለጹት መምህራን እና ሠራተኞች ዩኒቨርሲቲውን ተመራጭና ተወዳዳሪ ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁላችንም ተመሳሳይ ገጽ ላይ ሆነን በጋራ እንድሰራ እና በሳላፍነው ቅዳሜ ከተማሪዎች ጋር በነበረን ውይይት ወቅት የተነሱ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን አውቃችሁ ደካማውን የምናሻሽልበት ጠንካራውን ደግሞ በፍጥነት የምናሳካበትን የመፍትሄ ሃሳብ በጋራ ለመወሰን እንዲያስችለን ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በተማሪዎች የተነሱትን ሀሳቦች በማጠቃለል የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገ/ትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ልዩ ረዳት ዶ/ር ጀምበሩ ዓለሙ የተነሱትን ሀሳቦች በአስተዳደርና አካዳሚክ ዘርፍ በመለየት አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን የውይይት መነሻ ጽሁፍ መሰረት አድርገው መምህራን እና ሠራተኞች የተለያዩ ጥየቄ እና አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ እየመጣ መሆኑን የገለጹት አስተያት ሰጪዎች አሁን መሻሻል አለባቸው ብለን እያነሳናቸው ያሉ ጉዳዮች ቀላልና በአጭር ጊዜ ልንፈታቸው የምንችላቸው ነገሮች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመምህራን የኃላፊነት ውድድሮች በግልጽና ከአመራሮች ጋር በመመካከር የተሰራ መሆኑን የገለጹት የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገ/ትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓል ቦት መምህራንን በመቆጣጠር ረገድ ኃላፊነቱ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች መሆኑን ጠቅሰው የችግሩን ምንጭ በማጣራት የማስተካከያ እርምጃ አንደሚወሰድ አስገንዝበዋል፡፡ ውይቱንም እያካሄድን ያለነው ሁላችንም ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስላለብን ነው ብለዋል፡፡
ላቦራቶሪዎች ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምሩ ለተማሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጡና እየተሰራ ያለው ዝርዝር እቅድ እንደተጠናቀቀ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ተለይተው የማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናስ ከፍያለው በበኩላቸው ከተማሪዎች አገልግሎት አሰጣትና የግቢውበት እንዲሁም ከሰላምና ደህንነት ጋር ተገናኙ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ ሰጥተውባቸዋል፡፡
ከተማሪዎች ውይይት በኋላ የተስተካከሉ እና እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በጀትን በሚመለከት ሁሉም የስራ ክፍል ኃላፊ የተመደበውን በጀት አስከታች ድረስ ላሉ ሰራተኞችና መምህራን ማሳወቅ እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል፡፡ በአጠቃላይ የተነሱትን አስተያየቶች ተቀብለን የምንሰራባቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ሁላችሁም አብራችሁን እንድትሰሩ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት መሰራት የነበረባቸው ስራዎች ሳይሰሩ በመቅረታቸው ለዓመታት ተጠራቅሞ የቆየ ችግር እንደነበር ተገገልጿል፡፡
ተማሪዎች ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን መርጠው እንዲመጡ ሁላችንም የሚሰጡንን ስራዎች በተሰጠን ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ግንባር ቀደም ልንሆን ይገባል ካሉ በኋላ የተሰጡትንን አስተያየቶች ተቀብለን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስተካከል ኃለፊነታቸውን በማይወጡ ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ገልጸዋል፡፡