News Detail

ክስተቶች
Nov 03, 2025 308 views

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ የተማሪዎች የስነ-ምግባር አምባሳደርነት ውድድር አካሄደ

ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም)

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ የተማሪዎች የስነ-ምግባር የአምባሳደርነት ውድድር አካሂዷል።

ለተማሪዎችን ለማበረታታትና መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ በቦታው የተገኙት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ተወዳዳሪ ተማሪዎች ውድድሩን በማሸነፍና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባር አምባሳደር በመሆን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ እንዲሁም ተቋሙ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና አጋርነት ላይ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን በማስተዋወቅ ሌሎች ተማሪዎች ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን እንዲመርጡ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ወንድሙ የስነ-ምግባር መከታተያ ስራ ክፍል ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው ሙስናን መከላከል፣ ሙስና ተፈጽሞ ሲገኝ የፈፀመን አካል ወደ ህግ ማቅረብና የትውልድ የስነ-ምግባር ግንባታን ማስፈን መሆኑን ገልፀው በውድድሩ ከ1ኛ-3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች ሽልማት የተዘጋጀላቸው ሲሆን ሁሉም ከ1ኛ-10ኛ ደረጃ የወጡ ተወወዳዳሪዎች የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር መሆናቸውን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።

በተማሪዎች መካከል የተደረገውን ውድድር በዳኝነት የመሩት የስነ-ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህራን አቶ ዘላለም በፍቃዱና አቶ ተስፋዬ ባዬ እንዲሁም የስነ-ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ወንድሙ ሲሆኑ በወድድሩ ላይ ከተሳተፉት 20 ተማሪዎች መካከል ከ1ኛ -10ኛ ደረጃ የወጡ ተወዳዳሪዎች የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር ሆነው ተመርጠዋል። ከእነዚህም መካከል ተማሪ በለጠ ቦጋለ፣ ተመሪ ጋች ኮንግ እና ተማሪ ታገሰች ከበደ በቅደም ተከተል ከ1ኛ -3ኛ ወጥተዋል።

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባር መከታተያ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ወንድሙ የዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባር አምባሳደር ሆነው ለተመረጡ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ54 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ለሚደረገው ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል።

Recent News
Follow Us