News Detail

ክስተቶች
Feb 04, 2026 178 views

የኬንታኪ ግዛት ዩኒቨርሲቲ፣ የፍሎሪዳ የግብርና እና መካኒካል ዩኒቨርሲቲ (FAMU) እና የKALHER Hub ተወካዮች ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት(ጥር 27/2018 ዓ.ም)

የኬንታኪ ግዛት ዩኒቨርሲቲ፣ የፍሎሪዳ የግብርና እና መካኒካል ዩኒቨርሲቲ (FAMU) እና የKALHER Hub ተወካዮች ዓለም አቀፍ የአካዳሚክ አጋርነትን በሚያጠናክር መልኩ በጋራ ለመስራት ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት አካሂደዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ከኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ከፍሎሪዳ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርሲቲ እና ከካልሄር ማዕከል አጋሮቻችን ጋር በጋራ በተዘጋጀው በዚህ የህዝብ ንግግር ላይ ለመታደም ሁላችሁም ወደ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የአካዳሚክ ትብብር እና አጋርነትን ለማጠናከር በማሰብ ከአሜሪካ ረጅም ርቀት ተጉዘው የመጡ እንግዶችን አመስግነዋል።

ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ እንግዶች በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መገኘታቸው ከጉብኝት ባሻገር ለዓለም አቀፍ አጋርነት፣ ለእውቀት ልውውጥ እና ለትብብር ችግር አፈታት የጋራ ቁርጠኝነትን የሚያንፀርባርቅ መሆኑን ገልፀው ውስብስብ እና እርስ በርስ በተያያዙ ተግዳሮቶች በተቀረጸ ዓለም ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የሆኑ መፍትሄዎችን ለማመንጨት ድንበሮችን አቋርጠው መስራት አለባቸው ብለዋል።

አያይዘውም ዶ/ር ድሪባ የህዝብ ንግግር በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ እና በአለም አቀፍ አጋሮቻችን መካከል ያለውን ተቋማዊ ትብብር ለማጠናከር ትልቅ ምዕራፍ ያለው መሆኑን በመግለጽ የኬንታኪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና የፍሎሪዳ ኤ ኤንድ ኤም ዩኒቨርሲቲ እንደ ታዋቂ የምርምር ተቋማት በተግባራዊ ምርምር፣ በፈጠራ እና በማህበረሰብ ላይ ያተኮረ ልማትና የበለፀገ ልምድ የሚያመጣ ሲሆን በሌላ በኩል KALHER Hub የአካዳሚክ እውቀትን ከፈጠራ ሥነ-ምህዳሮች እና ከእውነተኛው ዓለም ተጽእኖ ጋር የሚያገናኝ ወሳኝ መድረክ ይፈጥራል።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓል ቦት በተማሪዎች የልምድ ልውውጥ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በዓለም ዓቀፍ ግንኙነተትና አጋርነት፣በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በማዕድን፣ በቱሪዝምና በግብርና ዘርፍ ጠንክሮ በመስራት ለክልሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚጠቅም ውጤት ማስገኘት እንዳለበት አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ምርምር፣ ዓለም አቀፋዊነትና አጋርነት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው በቀለ የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ፣ ዓላማና እሴቶች፣የልህቀት ማዕከላት፣የትምህርት ፕሮግራሞችን፣ከዩኒቨርሲቲው ጋር እሰሩ ያሉ አጋር አካላትን፣ የመምህራንን እና የተማሪዎችን መረጃ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

ከፍሎሪዳ የግብርና እና መካኒካል ዩኒቨርሲቲ (FAMU) ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ምቡያ ጥር 26/2018 ዓ.ም በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው አነቃቂና የስራ ተነሳሽነትን ይበልጥ ሊያዳብር የሚችል ሰፋ ያለ Public Lecture ለዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ለተማሪ ተወካዮች የሰጡ ሲሆን የኬንታኪ ግዛት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኮፊ ሲ. አካፖ፣ የKALHER Hub ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ተፈሪ ፀጋዬ፣የKALHER Hub መስራች አቶ መዝገቡ ዘሪሁን እና አቶ አቤል ቦጋለ መምህራን ዓለም አቀፍ ግንኙነትን እና አጋርነትን በማጠናከር፣ ለተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠትና የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ምርምሮችን በመስራት ዩኒቨርሲቲውን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ የረጅም ጊዜ ልምዳቸውን እና ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።

በተጨማሪም እነዚህ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታ ጥር 27/2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የአካዳሚክ አጋርነትን በሚያጠናክር መልኩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመስራት ተቋሞቻቸውን ወክለው ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርአት አካሂደዋል።

በተጨማሪም የውጭ ተመራማሪዎች ትምህርት ለሁሉም መሰረት መሆኑን በማስረዳት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ መሪ መሆን የሚችሉበትን ብሩህ ተስፋ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ የሶስቱ የውጭ ተቋማት ወኪሎችና ተመራማሪዎች በጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ተገኝተው ውይይት ያደረጉ ሲሆን የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ የጋምቤላ ናሽናል ፓርክን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም፣ የማዕድን፣ የግብርና እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተ ከአሜሪካ ለመጡ ተመራማሪዎች ከክልሉ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ገለፃ አድርገዋል።

በመጨረሻም ተመራማሪዎችና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየተሰራ ያለውን የአሳ እርባታ ፕሮጀክት ፖንድ እና በአቦቦ ወረዳ የሚገኘውን የአልዌሮ ግድብ ጎብኝተዋል።

Recent News
Follow Us