News Detail
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የክልል ሀብቶችን እና የተቋማዊ ምስልን በማስተዋወቅ ረገድ የተማሪዎችን ሚና አፅንዖት ሰጥተዋል
ጋምቤላ የባለ ብዙ ተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ክልል መሆኗን በማስተዋወቅ የዩኒቨርሲቲያችንን እና የክልሉን ገጽታ ልንገነባ ይገባናል ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ገለጹ::
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ በዛሬው ዕለት ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡ ተማሪዎች የምትማሩበትን ዩኒቨርሲቲ በመውደድና አምባሳደር በመሆን ክልሉ ያሉትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማስተዋወቅ ዩኒቨርሲቲያችን በተማሪዎች ተመራጭ እንዲሆን ሚናችሁ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም)
ዶ/ር ድሪባ እንደተናገሩት ጋምቤላ ክልል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገቡ ሁለት ባዮስፈር ሪዘርቨ የሚገኝባት፣ በሀገራችን ብቸኛው ለባህር ትራንስፖርተ አገልግሎት የሚውለው ባሮ ወንዝ የሚገኝበት፣ በሀገራችን 2ኛው ትልቁ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኝባት፣ በርካታ ወንዞችና ሀቆች የሚገኜባት፣ የተለያዩ የአሳና የአእዋፍ ዝርያዎች የሚገኙባት እንዲሁም የማዕድናት እና የለም መሬት ባለቤት መሆኗን ማስተዋወቅ ይገባናል ብለዋል፡፡
ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት የመማር ማስተማር መሰረት ልማቶች እያሟላ በመሆኑ ተማሪዎች ለላቦራቶሪ ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ጉዞ እና እንግልት ከመቅረቱም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው ካለአስፈላጊ ወጪ ይድናል፡፡ የተማሪዎች መውጫ ፈተና መጠነ ማለፍም ካለፉት ዓመታት የተሸለ ውጤት እንደተመዘገበ ገልጸው በዘንድሮው ዓመትም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተማሪ እንዲያልፍ በከፍተኛ ሁኔታ እተሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውሰዋል፡፡
ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሳይታለሉና የመጡበትን ዓላማ ሳይዘነጉ ከዛሬ ጀምሮ ጠንክረው በማንበብ የመውጫ ፈተና እንዲያልፉና በምርቃት ቀን ጋወን ለብሰው እራሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው እንዲደሰቱ ማድረግ እንደሚችሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞች ተማሪዎችን ለማገዝና ለመርዳት ሁሌም ዝግጂ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የለውጥ ጎዳና በማስፋት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን ወደ ከፍታ ማማ ላይ መውጣት ለማየት ከአመራሮቼ ጋር ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹ አሁን ያለው መሰረታዊ የተማሪዎች አገልግሎት ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር ብዙ መሻሻሎች መኖራቸውን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ለውጦች እያመጣ መሆኑን ዓይተናል ካሉ በኋላ ለመጣው ለውጥ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት እና አመራሮቻቸውን አመስግነዋል፡፡
ከተማሪዎች አገልግሎትና መማር ማስተማር ጋር ቴዩዞ በተማሪዎች በኩል የተለያዩ አስተያየቶና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ዘርፉ የሚመለከታቸው የስራ ኃለፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ እድል ሰጥተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የአስተዳደርና ቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናስ ከፍያለው ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ እንደሚሰጣቸውና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል፡፡
በመማር ማስተማር ዘርፍ ላይም የሚታዩ ጉድለቶችን ከመምህራን ጋር ውይይት በማድረግ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚፈቱትን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚደረግ የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ልዩ እረዳት እና ተወካይ ዶ/ር ጀምበሩ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ በተማሪዎች የተነሱ ነጥቦች በትክክል ተለይተው እንዲዙና በተዋረድ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሰራተኞችና መምህራን ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ስራ እንዲገቡ እንዲደረግ አሳስበው በቀጣይም ከተማሪዎች ጋር ውይይት የሚደረግበት ጊዜ እንደሚኖር አአሳስበዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ዲኖች ፣ ዳይሬክተሮች፣ ስራ አስፈጻሚዎች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡