News Detail

ገጽታ
Nov 01, 2025 187 views

በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተማሪዎች የህይወት ክህሎት ስልጠና እና የግብ አቀማመጥ

የዩኒቨርሲቲ ህይወት ዲግሪ የማግኛ መንገድ ብቻ ሳይሆን ማንነታችሁን የምታዉቁበትና በዚህ አለም ምን ልታበረክቱ እንደምትችሉ የምትማሩበት ተቋም ነዉ ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ ገለጹ፡፡

'ደስተኛ ህይወት መኖር ከፈለጋችሁ ህይዎትን ከሰዎች ወይም ከነገሮች ጋር ሳይሆን ከግብ ጋር አስተሳስሩ' ካሉ በኋላ ሴት ተማሪዎችም የነገ ህይዎታችሁን እጣ ፈንታ ማስተሳሰር ያለባችሁ ከሰዎችና ከጊዜያዊ ነገሮች ጋር ሳይሆን ከግባችሁ ጋር መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም)

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ሴቶች፣ ብሬክ ስሩ ትሬዲንግ አ.ማ እና የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ በመተባበር ለጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የህይወት ክህሎት ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ድሪባ ኢትቻ የራስን ግብ መቅረጽ ለጉዟችሁ አቅጣጫና ትርጉም ስለሚሰጥ ምን መሆን እንደምትፈልጉ፤ ምን ማግኘት እንደምትፈልጉ፤ የት መድረስ እንደምትፈልጉ ግልጽ ግቦችን በመቅረጽ መዘጋጀት ይኖርባችኋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች የወደፊት ሴት መሪዎቻችን መሆን እንዲችሉ ስኬታማ በሆኑ ክቡራን ሴት የህዝብ ተወከዮች ምክር ቤት አባላት ስልጠናዉ መቀናጀቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠዉ መሆኑን ጠቅሰው አመራሮቹ የእራሳቸዉን የህይወት ተሞክሮ ለተማሪዎች የሚያጋሩበት መልከም እድል ነዉ ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲያችን ሴት ተማሪዎች ስለግላችሁ ስኬት ብቻ ሳይሆን ሰፊዉን የህብረተሰባችን እና የሀገራችን ብሩህ የወደፊት ተስፋን የመቅረጽ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝባችሁ ስልጠናውን በንቃት እንድትከታተሉ ሲሉ አሳስበዋል።

ቁልፍ መልዕክት ያቀረቡት አቶ ቾት ኒት የክልሉ የህግ፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ጉዳዮች አማካሪ እና የጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ እንደገለጹት የህይወት ክህሎት በዕለት ተዕለት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት፣ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት፣ ከእራሳችን እና ከሌሎች ጋር ተስማምተን ለመኖርና ስኬታማ ህይወት ለመምራት የሚያበቃ ችሎታ መሆኑን ጠቅሰው ከስልጠና በተጨማሪ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመምህራን እና ከወላጆች መደበኛና መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሚዳብር ችሎታ ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ ሴቶች በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ብቁ በመሆን ስራ ፈጠሪ እንዲሆኑ በዙሪያቸው ያሉትን አማራጮች እንዲጠቀሙና እራሳቸውን በተለያዩ ክህሎቶች እንዲያበቁ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

ስልጠናው የእራስን ግብ መቅረፅ፣ የጊዜ አጠቃቀም እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ መንደፍ የሚሉትን ጉዳዮች ያካተተ ሲሆን የብሬክ ስሩ ትሬዲንግ ከፍተኛ የስልጠና ባለሙያ አቶ ሰመረ ነጋሽ ስልጠናውን ሰጥተዋል፡፡

የሰው ሀብት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ክብርት ወ/ሮ መናህል ኢምራን እና ክብርት ወ/ሮ ነጭቴ ፍላቴ የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች ኮከስ ስራ አስፈፃሚ እና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ መሪ ስራ አስፈፃሚ የህይወት ልምዳቸውን ለተማሪዎች አጋርተዋል፡፡

ከስልጠናው በኋላ ሴት ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ብዙ የተማሩበት እና ከዚህ በኋላ ለህይወታቸው ስኬት መሰረት እንደሚሆን ገልጸው አመራሮቹ ካጋሯቸው የህይወት ልምድ ጋር በማጣመርና ወደ ተግባር በመቀየር እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል፡:

Recent News
Follow Us